የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል ተዳራሽነትን ለማስፋፋት ባከናወናቸው ተግባራት በዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (On-Grid) እና ከግሪድ ውጪ (Off-Grid) በፀኃይ ኃይል አማራጮች 16 ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

አገልግሎቱ በ2019 ጥምት ወር ባከናወነው የኃይል መስመር ዝርጋታ ስራ፤ በዋናው መረብ (On-Grid) 15 ከተሞች እንዲሁም በኦፍ ግሪድ (Off-Grid) አማራጭ 1 ከተማ፣ በድምሩ 16 ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝተዋል።

አገልግሎቱ እነዚህን ከተሞች ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በዋናው መረብ 79 ነጥብ 05 ኪሎ ሜትር እና ከመረብ ውጪ 0 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር፣ በድምሩ 79 ነጥብ 41 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ አከናውኗል።

በተጨማሪም በዋናው መረብ 189 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር እና ከመረብ ውጪ 3 ነጥብ 95 ኪሎ ሜትር፣ በድምሩ 193 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ ሥራ ተከናውኗል።

ከትራንስፎርመር ተከላ ጋር በተያያዘ ለአገልግሎት ማሻሻያና ማስፋፊያ በዋናው መረብ 44 እና ከመረብ ውጪ 1፣ በድምሩ 45 ትራንስፎርመሮች ተተክለው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በአጠቃላይ በነዚህ ከተሞች አዳዲስ ደንበኞችን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በዋናው መረብ 4 ነጥብ 329 እና ከመረብ ውጪ 774፣ በድምሩ 5 ሺህ 103 የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች ተገጥመው ወደ ሥራ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዜጎችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ለመደገፍ የሚያደርገውን የመሰረተ ልማት ማስፋፋት አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡