የተቋሙ የተገልጋዮች ቻርተር እንደገና ተከልሶ ወደ ስራ ገባ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመኑ በሚጠይቀው የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራት ደንበኞችን ለማስተናገድ የተገልጋዮችን ቻርተር እንደገና በመከለስ ወደ ስራ አስገብቷል፡፡  ቻርተር

ቻርተሩን እንደገና መከለስ ያስፈለገው ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋና ጥራት ያለው፣ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ነው፡፡

የተገልጋዮች ቻርተር ዋና ዓላማ የደንበኞችን የመረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ፣ የተገልጋዮችን የባለቤትነት፣ የተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ደንበኞች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ እርካታ እንዲኖራቸው ለማድረግ እና የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ከተገልጋዮች ፍላጎት ጋር የተጣጣመ፣ ቀጣይነት ያለውና የተሻሻለ ለማድረግ ነው፡፡

ቻርተሩ የተቋሙን መብትና ግዴታዎች፣ የደንበኞን መብትና ግደታዎች እንዲሁም በተቋሙ በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡     

ቻርተሩ የባላድርሻ አካላት ሚና ምን እንደሆነ፣ የፍጆታ ሂሳብ መፈፀሚያ ዘዴዎችና አመራጭ መንገዶች፣ በ905 ነጻ የጥሪ ማዕከል ስለሚቀርቡ መረጃዎች፣ አዲስ ሃይል ጠያቂ ደንበኞች ማሟላት ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ የጉዳት ካሳ አከፋፍል እና ስለ ቅሬታ አቀራርብና አፈታት ስርዓት በዝርዝር የሚያብራራ ነው፡፡  

በተከለሰው የተገልጋዮች ቻርተር ደንበኞች አገልግሎት ፈልገው ሲመጡ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማወቅና አሟልቶ መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አዲስ ሃይል ፈላጊ ደንበኞች አገልግሎት ፈልገው ሲመጡ ለነጠላ ፌዝ ከሆነ የአመልካቾች የቀበሌ መታወቂያ፣ ፓስፖርት ወይም መንጃ ፍቃድና አንድ ጉርድ ፎቶ ግራፍ (3*4) ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ የኪራይ ቤት ከሆነ ከባለቤቱ የተሰጠ የስምምነት ደብዳቤ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጥያቄው ለሃይል ማሻሻያ ወይም ለተጨማሪ የሃይል ፍላጎት ከሆነ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ የመጨረሻ ክፍያ ደረሰኝ ማቅረብ ግድ የሚል ሲሆን፤ የሃይል ጥያቄው የሽርክና ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆኖ የሽርክና ማረጋገጫ ሰነድ ኮፒ ማቅረብ ይጠበቃል፡፡

የቀረበው ሃይል ፍላጎቱ ጥያቄ በመንግስት በሚተዳደሩ ቤቶች በሚኖሩ ነዋሪዎች ከሆነ በሚመለከተው የመንግስት አካል ሲፈቀድ እና ማንነቱን የሚገልፅ መታወቂያ ሲያቀርብ አገልግሎቱ የሚፈቀድለት ሲሆን ሃላፊነቱን የሚወስደውም ቤቱን የሚያስተዳድረው የመንግስት አካል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሃይል ጠያቂው የቀበሌ ቤት ተከራይነት ውል አያይዞ ካቀረበ አገልግሎቱን በተከራዩ ስም ሊሆን ይችላል፤ የአገልግሎቱ ሙሉ ሃላፊነትም የተከራዩ ይሆናል፡፡  

አገልግሎቱን የጠየቀው የግል ድርጅት ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት መስፈርቶች እንደተጠበቀ ሆኖ የድርጅቱን የምዝገባ የምስክር ወረቀት፣ የድርጅቱን ዋና ስራ አስኪጅ ማንነት የሚገልፅ መታወቂያ እና ለማስገመቻ የሚሆን 90 የኢትዮጵያ ብር መክፈል ይጠበቅበታል፡፡

የሚቀርበው ጥያቄ የሶስት ፌዝ እና የከፍተኛ ሃይል ከሆነ ለነጠላ ፌዝ ከቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች በተጨማሪ በባለስልጣን ወይም ኤሌክትሪክ ነክ የስራ ፈቃድ ባለው ተቋራጭ የተሰጠ የውስጥ ኤሌክትሪክ መስመር ምርመራ መጠናቀቅ ሚገልፅ የምስክር ወረቀት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

የሃይል ጥያቄው ከ14 ኪዋት በላይ ከሆነ የኤሌክትሪክ ዲዛይን ፕላን ማቅረብ የሚጠበቅበት ሆኖ አገልግሎቱን ለመስጠት ለሚደረገው የኢንስፔክሽንና የምርመራ ስራ የሚከፈለውን ክፍያ መፈፀምም አንዱ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ በዚህም ለባለ ሶስት ፌዝ ቆጣሪ 300 ብር፣ ከ24 ኪዋ እስከ 120 ኪዋ 500 ብር፣ ከ121 ኪዋ እስከ 1 ሜጋ ዋት 5000 ብር እና 1 ሜጋ ዋት በላይ 10000 ብር  መክፈል ይጠበቅበታል፡፡


Print   Email