ተቋሙ የጀመራቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጀመራቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የለውጥ አመራርና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው ገልፀዋል፡፡   174440130 4257345504277530 8498496713212213770 n

ተቋሙ በርካታ የለውጥ እንቅስቀሴዎችን በመተግበር ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ እሱባለው፤ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቀሴዎች ቀጣይነት ኖሯቸው በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተከታታይና ቀጣይነት ያላቸው የክትትልና ድጋፍ ስራዎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በአዲስ አወቃቀር ከተደራጀበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተሩ፤ ከእነዚህም መካከል በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው ያልተማከለ አደረጃጀት፣ የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ቴክኖሎጂ፣ አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ስታንዳርድ (IFRS)፣ የቋሚ ንብረት ቆጠራ እና ዋጋ ክለሳን (FAIR) ጨምሮ ሌሎች በርካታ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አሰራሮችን ተጀመረው ወደ ሥራ መገባቱ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ የክፍያ ስርዓቱን ለማሻሻል ከኢተዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር አማራጭ የክፍያ ስርዓት የዘረጋ ሲሆን፤ የቆጣሪ ንባብ ችግሮችን ለማቃለልም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ መደረጉን አንስተዋል፡፡

የለውጥ አመራርና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተቋሙ የጀመራቸውን አዳዲስ አሰራሮች በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ መደረጋቸውን፤ ተቋማዊ መመሪያዎች፣ ፕሮሲጀሮችና ፖሊሲዎች በአግባቡ መተግበራቸውን እና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ተከታታይና ቀጣይነት ያላቸው የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በሁሉም ክልሎች እያደረገ መሆኑንና በበጀት አመቱ ከ179 በላይ በሚሆኑ የስራ ክፍሎችና ማዕከላት በመስክ ምልከታ የክትትልና የድጋፍ ስራ መሰራቱን አቶ እሱባለው ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ተቋሙ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ፕሮሲጀሮች በአግባቡ መተግበራቸውንም በሚደረጉ የክትትልና ድጋፍ አግባቦች እና የሱፐርቪዥን ስራዎች ክትትል መደረጉንና የተገኙ ክፍተቶችንም እርምት እንዲደረግባቸው ለማድረግም ተችሏል ብለዋል፡፡

የተገልጋዮችን መብትና ግዴታዎች በአግባቡ ለማስረጽ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲቻል የተቋሙን የተገልጋዮች ቻርተር ዘመኑ በሚጠይቀው የአገልግሎት ፍጥነትና ጥራት መሰረት በመከለስ ወደ ትግበራ መገባቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ የሠራተኞችና የደንበኞችን ቅሬታ ለማስተናገድ ሚያስችል የቅሬታ ማቅረቢያ ስርዓት መዘርጋቱን እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱበት የአሰራር ስርዓት መኖሩን አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ባስቀመጠው መመሪያና የአሰራር ስታንዳርድ መሰረት አገልገሎት እየቀረበ መሆኑን የማረጋገጥ፤ በሚታዩ ክፍተቶችም ላይ የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡበት የማድረግ ስራ እንደሚከናወንና በተገኘው የመስክ ምልከታ ግብዓት ላይ የተቋሙ ከፍተኛ ማኔጅመንት ውሳኔ እንዲሰጥበትም ለማድረግ እንደሚሰራ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የተቋሙ የለውጥ አመራርና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የአሰራር ክፍተት በሚታይባቸው የስራ ክፍሎችን ስራዎች ላይ ሰፋ ያለ ጥናት በማድረግ የችግሩን ምንጭ የመለየት፣ የማስተካከያና የመፍትሄ አማራጭ ለማኔጅመንት ካውንስል እንዲቀርብ በማድረግም ዕገዛ የሚያደርግ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
የተገልጋዮችና የተቋሙ ሰራተኞች በተቋሙ አሰራር ላይ ያላቸውን የእርካታ ደረጃም ሆነ አስተያየት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በገለልተኛ አካል በማስጠናትም ጥንካሬና ድክመቶችን ለመለየት እና ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን እና የሰራተኞችን የአገልጋይነት ብቃት ለማሻሻል ተከታታይነት ያላቸው የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ከመሆኑም በተጨማሪ ሠራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት መፈፀማቸው ለመከታተል፣ ለመመዘንና ለመደገፍ የሚያስችል በሰራተኞች ብቃት ላይ ያተኮረ የአፈጻጸም ምዘና ስርዓት ለመዘርጋት ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ዳይሬክተሩ የተቋሙን ዓመታዊ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዕቅድ ከማሳካት አኳያ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ሪፖርቶችን በማሰባሰብ ለተቋሙ ከፍተኛ ስራ አመራር ቦርድ፤ ለሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየሶስት ወሩ የሚልክ መሆኑን በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል፡፡


Print   Email