በመጪው የኢድ-አልፈጥር በዓል የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ እየተሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው የኢድ-አልፈጥር በዓል የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ፤ ከተከሰተም አፋጣኝ ምላሽ ለመሰጠት እየሰራ ይገኛል፡፡
ተቋሙ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቆራረጥና ሳይዋዥቅ ለተጠቃሚው ለማቅረብ እንዲሁም ችግሩ ከተከሰተም በተገቢው መንገድ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉት የዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡184750212 4328150777197002 3050225531581998562 n
በተለይም ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ መቆራረጥ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በመለየት በመካከለኛና በዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ጭነት የማመጣጠንና ሌሎች የቅድመ-መከላከል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

 በዕለቱም በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የኃይል መቆራረጥ ቢያጋጥም አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚችል ግብረ-ሃይል በየደረጃው በሚገኙ የተቋሙ አደረጃጀቶች ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ከመቀነስ አኳያ ደንበኞች የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያላቸው ሲሆን፤ በቤት ውስጥ ሆነ በሥራ ቦታ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓታት በተለይ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዚያት ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡
የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች በበኩላቸው በዓሉ ሲደርስ የሚኖረውን አላስፈላጊ እንግልት ለማስቀረት እንዲችሉ ከወዲሁ የሚበቃቸውን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል አስቀድመው እንዲገዙ /ካርድ እንዲሞሉ/ ተቋሙ ከወዲሁ ያሳስባል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋማችንን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሞያዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ለስራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግም ይኖርበታል፡፡
ይሁንና የተቋሙ የጥገና ሰራተኞች በመምሰል መሠረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ህብረተሰቡ ይህንን ከወዲሁ ተገንዝቦ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን በመጠበቅ እንዲተባበርና እኩይ ተግባራት ሲገነዘብም ለሚመለከተው የህግ አካላትና ለተቋሙ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡
በመጨረሻም ድንገት የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም፣ ተቋሙን የሚመለከቱ ሌሎች መረጃዎች ለመጠየቅ እንዲሁም ጥቆማዎችና አስተያይቶች ለማቅረብ ወደ አቅራቢያቸው የሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ማሳወቅ ወይም ወደ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል እንደሚያስፈልግ እንጠቁማለን፡፡

Print   Email