ማዕከሉ ቤት ለቤት በመሄድ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አደረገ

Hits: 100

የባቱ ከተማ የደንበኞች አገልግሎት መሳጫ ማዕከል የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት የቤት ለቤት ቅስቀሳ በማድረግ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉን የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መስከረም ወንድማገኝ አስታወቁ፡፡

000save image

የማዕከሉ ሠራተኞች በሳምንት አንድ ጊዜ የመስክ የስራ ዘመቻ እንደሚያከናውኑ የገለፁት ወ/ሮ መስከረም፤ ከዘመቻው አንዱ የአዳዲስ ደንበኞችን ቁጥር ለማሳደግ ቤት ለቤት በመሄድ አገልግሎቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገኙ ማደረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በስብሰባዎችም ጭምር በመገኘት ደንበኞች በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠትና ውል በማዋዋል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል ብለዋል፡፡በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ ማዕከሉ 958 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን እንዲሁም ከፍለው ለሚጠባበቁ አዲስ ኃይል ጠያቂ ደንበኞች የአቅርቦት ችግር ካላጋጠመ ከ 4 ቀን ባልበለጠ ጊዜ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
 
የዚህ እድል ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞችም ይህንን በማረጋገጥ ተቋሙ ስለሰጣቸው አገልግሎት አመስግነዋል፡፡ማዕከሉ 14 ሺ 813 የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ያሉት መሆኑንና ከእነዚህም ውስጥ 523 የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች መሆናቸውን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡
 
ሁሉም ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችሉ ደንበኞች ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን በዘመናዊ የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም እየፈጸሙ እንደሚገኙ ስራ አስኪያጇ ገልፀው፤ ይህም የማዕከሉን የስራ ጫና ስለሚቀንስ ሌሎች ስራዎችን ለመከወንና የደንበኞችን ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ከዚህ ጎን ለጎን በከተማውና ዙሪያው ጥገና ለሚያስፈልጋቸው መስመሮች ክረምት ከመግባቱ በፊት የመለየትና ጥገና የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-
Print