በአፋር ክልል በገቢረሱ አዋሽ ፈንታሌ ወራዳ የሚኖሩ ከ500 በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳውቋል፡፡
የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው የተከናወነው በወረዳው በሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች ውስጥ ሲሆን፤ አርብሃራ ፣ ጉሩሙሊ እና ኤኤባ እንዲሁም በዱለቻ ወረዳ ቀበና የተባሉ አካባቢዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን አሊን ጨምሮ የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አመራሮች፣ የኣዋሽ ሰባት ከተማ ከንቲባ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
አቶ ያሲን አሊ አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፡- የአካባቢው ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በመንደራቸው እንዲገባላቸው ለተቋሙ ጥያቄ ካቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ ለነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በፕሮጀክት ቢሮ በኩል 2 ነጥብ 64 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር እንዲሁም 10 ነጥብ 24 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋት ሲከናወን መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም 8 ትራንስፎርመሮች ተከላ መከናወኑንና በአሁን ወቅትም ሥራው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አባህ አባ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በይፋ ካስጀመሩ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ለተደረገው ጥረት ተቋሙን አመስግነው፤ በወረዳው በተለያዩ ቦታዎች ለሚሰሩ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የአካባቢው ህብረተሰብ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው እአሳስበዋል።
ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-