የስድስቱ ከተሞች ፕሮጀክት አካል የሆነውና በሻሻመኔ ከተማ የሚከናወነው የኤሌክትሪክ መስመር መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ብሩክ ለማ ገልፀዋል፡፡
በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፤ በያዝነው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታሰብም በኮሮና ወረርሽኝና በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ መቆየቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን ሥራው በከፍተኛ ትኩረትና ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝና በቀጣይ በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡የፕሮጀክቱን ሰፊ ጊዜ የሚጠይቀው ከዲዛይን እስከ ምሰሶ ተከላ መሆኑን የገለፁት አቶ ብሩክ፤ እስካሁን 2 ሺህ 785 የዝቅተኛ እና 1 ሺህ 564 የመካከለኛ ኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎች መተከላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ይህም 82 ነጥብ 5 በመቶ አፈፃፀም ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
የሻሸመኔ ከተማ የመልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 81 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር እና 91 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ እንደሚሸፍን አቶ ብሩክ ጠቁመዋል፡፡ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በሀገራችን የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትን ተከትሎ የሚመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት እንዲሁም ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅን ለመቅረፍ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በመስመር ዝርጋታው በቀላሉ የማይጎዱና ለአደጋ የማያጋልጡ ኬብሎችን ጥቅም ላይ በማወልና ምሰሶዎቹም የኮንክሪት መሆናቸው ለረጅም አመታት በንፋስና በዝናብ የማይቆራረጥ የኃይል አቅርቦት መስጠት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት ለ100 ቋሚ ሰራተኞች እና ሌሎች ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በከተማው ከሚከናወኑ የሌሎች ተቋማት ፕሮጀክቶች ጋር የዲዛይን አለመጣጣም፣ የአንዳንድ ግለሰቦች በዲዛይኑ መሰረት በበራቸው አካባቢ ምሰሶ ለማስተከል ፈቃደኛ አለመሆን ለፕሮጀክቱ መጓተት መጠነኛ የሆነ ዕክል መፍጠራቸው አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡በመሆኑም ህብረተሰቡ ፕሮጀክቱ ለከተማውና አካባቢው የሚኖረው ፋይዳ እጅግ የላቀ መሆኑን ተገንዝቦ ሥራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚጠየቀውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርግ አቶ ብሩክ ጠይቀዋል፡፡
ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-